ሐምሌ 11/2013 (ዋልታ) – በማይካድራ በህወሓት ቡድን የተፈጸመው ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እጅግ አሰቃቂ እና ከአእምሮ በላይ እንደነበረ ገለጹ።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን ጥቅምት ወር ላይ የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝን በማጥቃቱ በተወሰደበት አጸፋ እርምጃ ቡድኑ በማይካድራ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችና ሌሎች በአካባቢው ለስራ የተሰማሩ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ በማድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ሲቪል ዜጎች መገደላቸው ይታወሳል።
አልጄዚራ የአይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ ከስፋራው ባሰራጨው ዘገባ ጭፍጨፋው እጅግ ዘግናኝ እና አረመኔያዊ ተግባር እንደነበር ዘግቧል።
በማይካድራ ነዋሪ የሆኑት አቶ ማሩ ገ/ማሪያም ከአልጄዚራ ጋር በነበራቸው ቆይታ አማራ በመሆናቸው ብቻ በርካታ ሰዎች መጨፍጨፋቸውን ገልጸው፤ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ እጅግ አሰቃቂ እና ከአእምሮ በላይ እንደነበረር ተናግረዋል፡፡
በዚህ በጥቅምት 2013 በተፈጸመ ጥቃት 600 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ቢገለጽም ነዋሪዎች ግን የሟቾች ቁጥር ከተባለው ሊበልጥ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በዘገባው የተካተቱት የአካባቢው ነዋሪ እናት በወቅቱ በልጃቸው የአካል ክፍሉ ላይ በደረሰበት ጥቃት መስማት የተሳነው ልጃቸውን አሳይተዋል፡፡
ከሟቾች ቤተሰብ መካከል አንዲት ባለቤቷ የተገደለባት ነዋሪ በበኩልዋ የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል ሲገድሉት ለምን ትገድሉኛላችሁ ምን አጠፋሁ እያለ ሲጮህ መስማቷን ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱ ከመፈጠሩ በፊት ከተለያዩ የአማራ ክልል ስራ ለመስራት ወደ ማይካድራ የተጓዙ ወጣቶች የተለያዩ ጥቃቶች ይደርሱባቸው እንደነበረም ዘገባው ጠቁሟል።
በአሁኑ ሰአት ቦታው በአማራ ልዩ ሃይልና በፌዴራል መንግስት ሃይሎች ቁጥጥር ስር በመሆኑ ሰላሙ ተረጋግጦ እንደሚገኝ በዘገባው ተመላክቷል፡፡
ከኢትዮጵያ ተሰደው በሱዳን መጠለያ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች የፌደራል መንግስት ሃይሎች እንዲወጡ እንዳስገደዱዋቸው ቢናገሩም በውስጣቸው የማይካድራ ጭፍጨፋ የተሳተፉ አካላት እንዳሉ አልጀዚራ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ማሩን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ምርመራ አድርጎ ባወጣው መረጃ መሰረት በቦታው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመ ማረጋገጡን ሪፖርት ማድረጉን የኢዜአ ዘገባ አስታውሷል።