የካቲት 19 /2013 (ዋልታ)- የፖለቲካ ፓርቲዎች በምረጡኝ ቅስቀሳቸው በሚዲያ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ግጭትና ጥላቻ ቀስቃሽ እንዳይሆኑ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው የምርጫ ስነ-ምግባር መመሪያውን መርህ በመከተል አማራጭ ፖሊሲዎቻችንን ለሕዝብ እናቀርባለን ብለዋል።
በ6ኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የተመዘገቡ ፓርቲዎች የቅስቀሳ መርሃ ግብር ከየካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ መካሄድ ጀምሯል።
በዚሁ መሰረት ፓርቲዎች በምረጡኝ ቅስቀሳ መርሃ ግብራቸው አማራጭ ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለሕዝብ ተደራሽ እያደረጉ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን በሚያካሂዱት ቅስቀሳ የምርጫ መመሪያውን እንዲከተሉና የሰለጠነ የፖለቲካ ስልት እንዲያራምዱ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም አሳስበዋል።
በመሆኑም በቀጣይ በሚደለደለው የአየር ሠዓት ፓርቲዎች በተለያዩ ጉዳዮች የያዟቸውን አማራጭ ፖሊሲዎች ለሕዝቡ በማስተላለፍ የተመደበላቸውን ጊዜ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።