በምክር ቤቱ የሪፎርም ስራ ለተሳተፉ ምሁራን እውቅና ተሰጠ

ሐምሌ 22/2013 (ዋልታ) – በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሪፎርም ስራዎች ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምሁራን እውቅና እና ሽልማት ተሰጣቸው፡፡

ምክር ቤቱ ካከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች መካከል የህግ ማርቀቅ ስርዓት ጥራትን የሚያስጠብቅ ማንዋል ዝግጅት ሲሆን፤ በዛሬው እለት እውቅና የተሰጠቸውም በዚህ ማንዋል ዝግጅት የተሳተፉ የህግ ምሁራን ናቸው፡፡

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የእውቅና የምስክር ወረቀትና ሽልማቱን ባበረከቱበት ወቅት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ መስራት በመቻሉ ምክር ቤቱን ለማዘመን የሚያስችሉ በርካታ ግብኣቶችን ማግኘት ስለመቻሉ መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

እውቅና እና ሽልማት የተሰጣቸው ዶክተር ኤሊያስ ኑር፣ አቶ ሽፈራው ወ/ሚካኤል፣ አቶ ዘነበ ቡልቃ እና አቶ አቶ ዘካሪያ ኤርኮላ ሲሆኑ፤ ምክር ቤቱ ለሰጣቸው እውቅና ምስጋና በማቅረብ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የተዘጋጀውን ሰነድ የተለያዩ ዘመናዊ አማራጮችን በመጠቀም ተደራሽ ማድረግ ቢቻል፣ ማንዋሉን በአግባቡ መጠቀም ይቻል ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢ ስልጠና እንዲያገኙ ቢደረግ እንዲሁም በቂ ልምድና ፍላጎት ያላቸው ባለሙያዎች የህግ ማርቀቅ ሂደቱ ላይ እንዲሳተፉ ቢደረግ የሚሉት ከምሁራኑ የቀረቡ አስተያየቶች ናቸው፡፡

የቀረቡትን አስተያየቶች እንደሚቀበሉ የገለጹት  አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ምክር ቤቱ ባስጠናው አዲስ አደረጃጀት የህግ ማእከል ማቋቋም እንደሚገኝበትና ማእከሉ ሲቋቋም በርካታ ችግሮች እንደሚፈቱ ጠቁመዋል፡፡