በምዕራብ ሀረርጌ ገመቺስ ወረዳ የሚገኘው ወለንሶ ተፋሰስ ልማት ተጎበኘ

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ የተመራው ልዑክ ቡድን በምዕራብ ሀረርጌ ገመቺስ ወረዳ የሚገኘውን ወለንሶ ተፋሰስ ልማትን ጎበኘ።

ባለፉት ዓመታት በገመቺስ ወረዳ የተለያዩ የተፋሰስ ልማቶች ሲሰራ መሰንበቱ የተገለፀ ሲሆን ይሄንኑ በማስቀጠል ዘንድሮም በወረዳው በተለያዩ ስፍራዎች በተሰሩት የተፋሰስ ልማቶች የአከባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህ ስፍራ ላይ ከዚህ ቀደም የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ባለመሰራታቸው የአከባቢው ማኅበረሰብ ለድርቅ ሲጋለጥ እንደነበር የገለፁት የገመቺስ ወረዳ ነዋሪዎች በዚህም ምክንያት ብዙዎች ከአከባቢው ለመፈናቀል ተገደው ነበርም ብለዋል።

ይሁንና ከዓመታት ወዲህ ይህ የተፋሰስ ልማት ሥራ መሰራት ከተጀመረ ወዲህ ግን ጥሩ አየር ከማግኘት ባለፈ ዘርተውም አመርቂ ሰብል እየሰበሰቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አበራ ወርቁ የተመራው ልዑክ ቡድን በምዕራብ ሀረርጌ የሚገኙትን የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በመጎብኘት ለሌላው እንደ ግብዓት ይሆን ዘንድ ልምድ የመቅሰም ፕሮግራምን እያካሄዱ ይገኛሉ።

በታምራት ደለሊ