በምዕራብ ወለጋ ዞን የጊምቢ፣ ጃርሶ እና ቦጂ ጮቆርሳ ነዋሪዎች የኦነግ ሸኔ ሽፍቶች በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ያደረሱትን እና እያደረሱ ያሉትን ጥፋት በላማዊ ሰልፍ አውግዘዋል።
በጊምቢ ወረዳ የጆጊር እና ቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች የኦነግ ሸኔን ጥፋት አውግዘው፣ በሕዝቡ ላይ ከባድ ጥፋት የፈፀመውን የሽፍታ ቡድን እና ይህን ቡድን የሚያግዝን አካል ኅብረተሰቡ እንዲያጋልጥ ጠይቀዋል።
በዞኑ የጃርሶ ወረዳ ነዋሪዎችም “ኦነግ ሸኔ የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት ነው፤ የኦሮሞን ሕዝብ አይወክልም፤ የሰላም እና የልማታችን እንቅፋት ነው” የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮችን በመያዝ የቡድኑን የጥፋት ድርጊት በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውመዋል።
የወረዳው የአስተዳደር እና የሰላም ጽ/ቤት ተወካይ አቶ አበበ ኢታና፣ ኦነግ ሸኔ በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት እያወቀ ለዚህ ቡድን ድጋፍ የሚያደርግ የትኛውም አካል ተጠያቂ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የቦጂ ጮቆርሳ ወረዳ ነዋሪዎች በተመሳሳይ ቡድኑን ያወገዙ ሲሆን ከዚህ በኋላ የዚህን የጥፋት ቡድን ድርጊት የማይታገሱ መሆኑን ገልጸዋል።
የወረዳው አስተዳደር አካላትም ከሕዝቡ ጋር ተመሳስለው በጎን የኦነግ ሸኔን የጥፋት ቡድን የሚደግፉ አካላት ከድርጊታቸውን እንዲቆጠቡ ማሳሰባቸውን ኦቢኤን ዘግቧል።