በምዕራብ ጎጃም 42 የህወሓት እና ኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ነሀሴ 21/2013 (ዋልታ) – በምዕራብ ጎጃም ዞን 42 የህወሓት እና ኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ፡፡
የአሸባሪው ህወሓት እና የኦነግ ሸኔ የጥፋት ቡድኖች እስከሚደመሰሱ ሕዝቡ የጀመረውን ጠላትን የመመከት እና የመቅበር ዘመቻ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር ወቅታዊ የሕልውና ዘመቻን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ አሸባሪው ህወሓት በመላው የአማራ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደቀነውን አደጋ ለመመከት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የሕልውና ዘመቻ እያካሄደ ነው፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ስሜነህ አያሌው በመግለጫቸው እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት እና የእርሱ ቅጥረኞች የከፈቱትን ጦርነት ለመመከት መንግሥት ያቀረበውን የክተት ጥሪ መነሻ በማድረግ የዞኑ ሕዝብ ግንባር ከመዝመት ጀምሮ ለሕልውና ዘመቻው ሀብት በማሰባሰብ ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡
ዞኑ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አዋሳኝ መሆኑን ተከትሎ ከእነዚህ አካባቢዎች የሚመጣን የአሸባሪው ህወሓት ቅጥረኛን ትንኮሳ መመከት የሚያስችል የጸጥታ ሃይል በበቂ ሁኔታ መሰማራቱን ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል፡፡
በተደረገው የሰርጎ ገብ ፍተሻም በዞኑ 174 ጸጉረ ልውጦች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ሲካሄድ ቆይቷልም ነው ያሉት፡፡
በተደረገው ምርመራም 42ቱ በተጨባጭ የአሸባሪው ህወሓት እና የኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድንን ተልእኮ ይዘው ወደ ዞኑ መግባታቸው መረጋገጡን ጠቅሰው፣ በቀሪዎቹም ላይ ምርመራ መቀጠሉን ተገልጿል፡፡
እስካሁን እየተደረገ ባለው የሕልውና ዘመቻ የአሸባሪው አከርካሪ እየተሰበረ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሞ ሕዝቡ ወደ ልማት እስከሚዞር የዞኑ ሕዝብ ለሕልውና ዘመቻው የሚያደርገውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።