ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) በደቡብ ሱዳን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠላም ማስከበር ጥላ ስር የሚገኙ ከ120 ሀገራት በላይ የተሳተፉበት የባህል ትውውቅ ፌስቲቫል ተካሄደ።
ጁባ የሚገኘው የኢትዮጵያ 15ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ የባህል ቡድንም በባህል ትውውቅ ፌስቲቫሉ ላይ የኢትዮጵያን ባህል በሚገባ በማስተዋወቅ ሽልማት ተበርክቶለታል።
በባህል ትውውቅ መድረኩ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ሽልማቱን ያበረከቱት በደቡብ ሱዳን የተሰማራ ሰላም አስከባሪ ሃይል የበላይ ጠባቂ ጀነራል ኒኮላስ ሃይከን ባስተላለፉት መልዕክት በሠላም የማስከበር ተልዕኮ ተሳታፊ የሆኑ ሃገራት በግዳጅ አፈፃፀማቸው የተሻለ ውጤት በማምጣት ቀጠናው የተረጋጋ እንዲሆን ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል።
የየሃገራቱ ሠራዊት ከግዳጃቸው በተጓዳኝ የባህል ትውውቅ መድረክ በማዘጋጀት አምባሳደርነታቸውን በተግባር አስመስክረዋልና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።
የሠላም አስከባሪ ኃይሉን ይበልጥ የሚያቀራርቡ መሠል መድረኮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ያሉት በደቡብ ሱዳን የተሰማራ ሰላም አስከባሪ ሃይል (የዩናሚስ) የበላይ ጠባቂው የባህል ትውውቁ የሠላም አስከባሪ ሀገራቱን ወዳጅነት ለማሳደግ ስለሚረዳ ይበልጥ ሊጎለብት እንደሚገባ መጠቆማቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል፡፡