በሥራ ቦታ የሚፈጠሩ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል ያለመ ውይይት ተካሄደ

የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ

በሥራ ቦታ የሚፈጠሩ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል ያለመ ውይይት ተካሄደ፡፡

የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በስራ ቦታ ላይ ሠራተኞች ራሳቸውን እንዴት መጠበቅ አለባቸው በሚል በተዘጋጁ ሁለት ጥናቶች ዙሪያ ከባለድርሻ ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

ጥናቶቹ በሥራ ቦታ የሚፈጠሩ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል ያለመ ነው ተብሏል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 6 ሺህ 300 የሚደርሱ ሰዎች በቀን ውስጥ በስራ ላይ በሚፈጠሩ አደጋዎች ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡና ከዚህም 550 ሰዎች ቆይቶ በሚፈጠሩ የሙያ ላይ በሽታዎች እንደምያዙ በጥናቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያ በባህርዳር፣ ኮምቦልቻ እና ትግራይ ጨርቃጨርቅና ጋርሜንት ኢንዱስትሪዎች በተካሄደው ጥናት 7 ሺህ 992 ሰዎች አደጋ እንደምደርስባቸውና ለህክምና ወደ ሆስፒታል እንደሚሄዱ ተገልጿል፡፡

5 ሺህ 276 ሰዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጤናማ ባልሆነ የስራ አካባቢ በመኖሩ ምክንያት አደጋ እንደምደርስባቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በስራ ቦታዎች አደጋዎችንና የሙያ በሽታዎችን ለመቀነስ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ለዋልታ ገልጸዋል፡፡

በዚህም በኢንዱስትሪዎች እና ፋብሪካዎች የሚከሰተውን በሽታ ለመከላከል ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ጥናቶች ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በስራ ላይ አደጋዎችንና ከሙያ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ በሽታዎችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ክፍተት እንዳለው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ችግሮችን እንዴት መፍታት ይቻላል በሚል በተካሄደው ጥናት ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ትምህርት ክፍል ዲን እና መምህር ፕሮፌሰር ዳመነ ኃይለማሪያም በበኩላቸው፣ በስራ ቦታ ሰራተኞች ጤና እንዲጠበቅ ኢንዱስትሪዎች እና ፋብሪካዎች ለሰራተኞች ምቹ እንዲሆኑ ከሚኒስቴሩ ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዳመነ ኃይለማሪያም

ጤናማ ሰራተኛ እንዲኖር ኢንዱስትሪዎች ምቹና ጤናማ አካባቢ መፍጠር ይኖርባቸዋል ያሉ ሲሆን፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ዙሪያ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተውበታል፡፡

(በአድማሱ አራጋው)