በሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ “ልዩ ምልከታ” የተሰኘ የውይይት መድረክ ተጀመረ

የካቲት 11/2014 (ዋልታ) ብሩህ ማይንድስ ኮንሰልት የተሰኘ ድርጅት ያዘጋጀና በሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረት ያደረጉ ተከታታይ የውይይት መድረክ ተጀመረ።

በዛሬው ዕለትም በኢትዮጵያ የኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ጥረቶች፣ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች በሚል ዕስ የመጀመሪያው መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ በሥራ ፈጠራ ልምድ ያላቸው ግለሰቦች ለጀማሪ ወጣቶች ልምዳቸውን አካፍለዋል።

በድርጅቱ የፕሮግራም አስተባባሪ ለማወርቅ ደቅሲሳ ሥራ አጥነትና የገቢ አለመመጣጠንን ችግር ለመፍታት የሕግ፣ የፖሊሲ፣ ተቋማዊ ቢዝነስ ልማት ሁኔታዎች መመቻቸት ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል።

የአገሪቱ ነባረዊ ሁኔታን በማገናዘብ ችግሮችን ለመቋቋም አሁን ላይ ከሚስተዋሉ የተበታተኑ ጥረቶች ይልቅ የተቀናጀ የግል ዘርፉንና የመንግሥት ጥምረትን በማበረታታት አስቻይ ከባቢ መፍጠር አስፋለጊ ነው ብለዋል፡፡

የሥራ እድል እጥረትን ለመቅረፍ በመንግሥት፣ በልማት አጋሮች፣ በምግባረ ሰናይ ድርጅቶቸና በግሉ ዘርፍ መጠነ ሰፊ ጥረቶች ቢደረጉም አሁንም በቢዝነስ ልማት ማበረታት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ሰፊ የሆነ ከፍተት መኖሩን የፕሮግራሙ አስተባባሪ አንስተዋል።

በብርሃኑ አበራ