በሩስያ የኢትዮጵያ ወዳጆች ማህበር ዓመታዊ ክብረበዓሉን አካሄደ

ከኢትዮጵያ ጋር በልዩ ልዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ወዳጅነት እና ትውውቅ ባላቸው ሩስያውያን እና በሩስያ የኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ አባላት የተመሰረተ በሩሲያ የኢትዮጵያ ወዳጆች ማህበር በአዲስ መልክ ተጠናክሮ የተቋቋመበትን ዓመታዊ ክብረበዓሉን አካሄደ፡፡

በዝግጅት ላይ የተገኙት በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ከሩሲያ ለዘመናት የቆየ ጠንካራ ግንኙነት ያላት ሀገር በመሆኗ በርካታ ሩስያዊያን ወዳጆች ማፍራቷን አውስተዋል፡፡

የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ብዙ ልምዶች እና ተሞክሮዎቻቸውን ሲለዋወጡ የኖሩ መሆናቸውንና ለዚህም የወዳጅነት ማህበራት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አምባሳደሩ የወዳጅነት ማህበሩ ወደፊትም በሳይንስ፣ በንግድ፣ በትምህርት እና በኢንቨስትመንት መስክ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠነክር የበኩሉን እንዲያበረክት ጠይቀዋል።

በመቀጠልም አምባሳደር አለማየሁ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ እና ተጨባጭ ሁኔታን በሚመለከት በሰጡት መግለጫ፣ በሀገሪቱ በሰሜኑ ክፍል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ፣ ዘመቻውን ተከትሎ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የመልሶ ግንባታ ስራዎችና የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ ርብርብ፣ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ በሚመለከት እንዲሁም ከጎረቤት ሱዳን ጋር ስላለው የድንበር ጉዳይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የማህበሩ አባላትም በተደረገላቸው ገለፃ ዙሪያ ትክክለኛ መረጃ በመያዝ በሚያገኙት አጋጣሚ ሀሉ ይህንን ተጨባጭ እውነታ ለሌሎች ወዳጆች እና አጋሮች እንዲያስገነዝቡ አምባሳደር አለማየሁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሩሲያ የኢትየጵያ ወዳጆች ማህበር ሰብሳቢ የሆኑት ወይዘሮ ታትያና ዡልቬ በበኩላቸው ማህበሩ በሩሲያ እና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል የቆየውን ታሪካዊ ወዳጅነት እና ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ የሚያሳዩ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የወግ ዕቃዎች፣ ቋንቋ፣ ባህላዊ አልባሳት፣ ባህላዊ ምግቦች በሩስያውያን ዘንድ ይበልጥ እንዲታወቁ ተወዳጅ እንዲሆኑ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡

በወቅቱም ከሩሲያ ሳይንስ አካዳሚ የመጡ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ስለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለታዳሚዎች ገለፃ አድርገዋ፡፡

በተጨማሪም ስለኢትዮጵያ የፊደል ገበታ፣ ባህላዊ ጭፈራዎች እና ሙዚቃዎች ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ዝግጅት ቀርቦ አድናቆትን ማግኘቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡