በራያ ቆቦ የሮቢት 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት 19 የተናጠልና የጅምላ መቃብሮች ተገኙ

ታኅሣሥ 22/2014 (ዋልታ) በራያ ቆቦ ወረዳ በሚገኘው የሮቢት 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት 19 የተናጠልና የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውን ተገለጸ፡፡

የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ መንገሻ በላይነጋ እንደገለጹት በሮቢት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ከተገኙት 19 መቃብሮች 3ቱ በእያንዳንዳቸው እስከ 30 ሰዎች የተቀበሩባቸው የጅምላ መቃብሮች ናቸው።

የአሸባሪው ትሕነግ ወራሪው ቡድን የወረዳውን ትምህርት ፅህፈት ቤት እና በወረዳው የሚገኙ 7 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ 129 ትምህርት ቤቶችን በመውረር ዘረፋ መፈጸሙንና ንብረቶች ማውደሙን ኃላፊው ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ከዘረፋቸውና ካወደማቸው ንብረቶችና ቁሳቁስ መካከልም የቤተ ሙከራ ቁሳቁስ፣ ኮምፒውተሮች፣ ፕላዝማዎች፣ የተማሪ ሰነዶችና ሌሎችም የትምህርት ቤቱ ንብረቶች ይገኙበታል።

የሮቢት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጥበቃ ሰራተኞች አቶ ይመር አየለና ዝናቡ ሰማው ወራሪው ቡድን ትምህርት ቤቱን የመቃብር ስፍራ እንዳደረገው መናገራቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የሮቢት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ከ1ሺሕ 800 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር እንደነበርም ተገልጿል።