በራያ ወረዳ የሽብር ቡድኑ ንፁሃንን ሲጨፈጭፍ ባለቤታቸውን ያጡት እናት
በምንይሉ ደስይበለው
ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ሁሉ ይቃወሙኛል፤ መንግሥትን ይደግፋሉ የሚላቸውንና ወጣቶችን በጅምላ ረሽኗል። በዋጃ ከተማም ይህንን ድርጊት ፈፅሞታል።
የወይዘሮ ፍሬወይኒ ፈንታሁን ባለቤት መንገሻ ተፈራም የትሕነግ ወራሪ ኃይል የግፍ ጭፍጨፋ ሰለባ ሆነው አልፈዋል።
ወይዘሮ ፍሬወይኒ የ13 ዓመት የትዳር አጋራቸው ከመንገድ ላይ ተጠልፈው በመወሰዳቸው ፍለጋ ተንከራተዋል፡፡
ባለቤታቸው ከሞቱ ከ33 ቀን በኋላ ነው በግፍ ተገድለው ከተቀበሩበት ቦታ አስከሬናቸው መጥቶልኝ ባለቤቴን የቀበርሁት ሲሉ ነው የሽብር ቡድኑን የግፍ ጥግ የሚያስረዱት።
በንግድ ስራ ይተዳደሩ የነበሩትና በትሕነግ በግፍ የተገደሉት መንገሻ ተፈራ ከባለቤታቸው ፍሬወይኒ ጋር 3 ልጆችን አፍርተዋል። ዛሬ ላይ ስራ የሌላቸው የሟች ባለቤት ልጆቼን ለማሳደግ ከብዶኛል ሲሉም ሀዘን በሰበረው አንደበት ለዋልታ ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ትሕነግ ሐምሌ 16 ወደ አካባቢው ሰርጎ በገባበት ወቅት ታፍነው የተወሰዱት መንገሻን ለመፈለግ ወንድማቸው አዳነ ብዙ ቀናትን አስክሬን ፍለጋ ተንከራተዋል።
የትሕነግ የግፍ ግድያ ሰለባ የሆኑትን መንገሻ ለብሰው የነበሩትን የሽርጥ ምልክትና ፎቶ ግራፍ በመያዝ ትሕነግ በግፍ ጨፍጭፏል በተባለበት ቦታ ሁሉ ወንድማቸውን ፍለጋ ተዟዙረዋል።
የወንድማቸውን አስክሬን በሥርዓቱና በወጉ ለመቅበር ፍለጋ ላይ እያሉ ራያ ወረዳ ቀበሌ 28 ሰንደዶ የምትባል ቦታ በሽብር ቡድኑ በየበርሃውና እርሻ ማሳው ላይ የተጨፈጨፉ ንፁሃን አስክሬን ተቀብሯል ሲባል ሲሰሙም ወደቦታው አቅንተዋል።
በሽብር ቡድኑ የክፋት ጥግና የጭፍጨፋ ድርጊቱ ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። የመንገሻ ተፈራ አስከሬን ተቀብሮ በተገኘበት አካባቢ ሌሎች የንፁሃን ቀብር ይገኛል።
ይህም የሽብር ቡድኑ ንፁሃንን ከመጨፍጨፍ ባሻገር ከአላማጣ እስር ቤትና በህክምና ላይ የሚገኙ ወታደሮችን ወደ በረሃውና እርሻ ማሳው ላይ በማምጣት የረሸነበት እንደሆነ ዋልታ በስፍራው ተገኝቶ በሰበሰባቸው መረጃዎች ተረድቷል፡፡
ራያ ወረዳ ቀበሌ 28 ነዋሪ የሆኑት ቄስ ፈንቴ ንጉሤ በአካቢያቸው በርካቶች ተገድለው እንደተመለከቱ በማስቀደም፤ በግፍ ተገድለው የተቀበሩበትን ስፍራ ለዋልታ አሳይተዋል።
የሽብር ቡድኑ በግፍ ከመግደሉ ባሻገር ማኅበረሰቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና ለማድረስ በሚል ለማሸበር የገደላቸውን ንፁሃን እንዳይቀበሩ በማድረግም እስከ 6 ቀን ድረስ አስክሬናቸው ፀሀይ እንዲመታው አድርጓል።
የትሕነግ የሽብር ቡድን ከራያ አካባቢ ብዙ ሰዎችን እያፈነ ወስዷል። በርካቶችም በግፍ ተጨፍጭፈዋል። ወይዘሮ ፍሬወይኒ ባለቤታቸው ከተቀበሩበት የእርሻ ማሳ ላይ አስወጥተው እምነቱና ባህሉ በሚፈቅደው ማስቀበር ቻሉ እንጅ በዙዎቹ የግፍ ጭፍጨፋ ሰለባዎች ማንነታቸው ያልታወቀ በመሆኑ በየመንገዱና በየበረሃው ተቀብረው ቀርተዋል።