በሰሜን ሸዋ ዞን የህብረተሰቡን ሠላም ለማናጋት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 25 የጥፋት ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

ሰኔ 18/2015 (ዋልታ) በሰሜን ሸዋ ዞን ከነፍስ ወከፍ እስከ ቡድን መሣሪያ ዲሽቃ በመታጠቅ የህብረተሰቡን ሠላም ለማናጋት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የጥፋት ቡድን አባላት በዞኑ ፀጥታ ኃይልና በመከላከያ ሠራዊቱ የተቀናጀ ዘመቻ እኩይ ዓላማቸውን ለመፈፀም እየተማከሩ ባሉበት ድንገት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።

በቁጥጥር ሥር የዋሉት የቡድኑ አባላት ቁጥር 25 ሲሆን ከዚህ ቀደም የመከላከያ ሠራዊት እና የልዩ ኃይል አባል የነበሩ በኅቡዕ ሴራቸውን ለማስፈፀም በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ተታለው ጫካ የገቡ ወጣቶች መሆናቸው ተገልጿል።

የሰሜን ሸዋ ዞን የፀጥታ ኃይል ክትትል እያደረገ ባለበት ወቅት የጥፋት ቡድኑ አባላት ተኩስ በመክፈታቸውና የከፋ ጉዳት ሊያደርሱ በመሆኑ በቀጠናው ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት አስቸኳይ ሪፖርት በማድረግ በፍጥነት በቦታው ላይ በመድረስ መቆጣጠር መቻሉ ተጠቅሷል።

የሠላም ፀር የሆኑ እነኝህ የቡድኑ አባላት የግለሰብ ቤት በመከራየት በሚሰጣቸው ተልዕኮ መሠረት የጥፋት ተግባራቸውን ለመፈፀም 1 ዲሽቃ፣ 2 ብሬን፣ 4 ስናይፐር፣ 5 ክላሽ፣ 2 ሽጉጥና ከ2,300 በላይ ተተኳሽ ጥይቶችን እንዲሁም ጥሬ ገንዘብና ግማሽ ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ያለው የባንክ አካውንት ይዘው ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት መረጃ አመላክቷል።

የጥፋት ቡድኑን አባላት በፈጣን ክትትል መቆጣጠር ባይቻል ኖሮ በሕብረተሰቡ ላይ ጥፋት ያደርሱ እንደነበር የገለፁት የፀጥታ ኃይል አባላት፤ የሕዝቡን ሠላም ለማስጠበቅ አበክረው እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሕግ ጥላ ሥር የዋሉት ግለሰቦችም አብዛኞቹ ተታለው እንደገቡና ሕገ ወጥ አደረጃጀት ፈጥረው መንቀሳቀሳቸውን በማመን ወጣቶች ከእንደዚህ ዓይነቱ ዓላማ ከሌለው ተግባር መቆጠብ እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።