በሰሜን አሜሪካ የአትሌቶች ማህበር አባላት ለ “ጽዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” ኢንሼቲቭ 8 ሺሕ 300 ዶላር ድጋፍ አደረጉ

ግንቦት 30/2016 (አዲስ ዋልታ) በሰሜን አሜሪካ የአትሌቶች ማህበር አባላት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት ለተጀመረው “ጽዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” ኢንሼቲቭ 8 ሺሕ 300 ዶላር የገንዘብ እና አንድ መጸዳጃ ቤት ለመስራት የአይነት ድጋፍ አደረጉ።

የማህበሩ ተወካዮች ዋሽንግተን በሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ በመገኘት ድጋፋቸውን በአሜሪካ የኢትየጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) አስረክበዋል።

የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት ኃይሉ መኮንን አገራቸው በምትፈልጋቸው ወቅት ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደሩም የማህበሩ አባላት በተለያዩ አገራዊ ጥሪዎች ላይ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው አሁንም ማህበሩ ለ”ጽዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” ኢንሼቲቭ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን በዋሽንግተን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል።

በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ለ”ጽዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” ኢንሼቲቭ እስከአሁን በአጠቃላይ በዓይነት 21 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ 14 መጸዳጃ ቤቶችን ለመስራት ቃል የገቡ ሲሆን በጥሬ ገንዘብ 29 ሺሕ 445 የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም 74 ሺሕ የኢትዮጵያ ብር መሰባሰቡ ተገልጿል።