በሰሜን ወሎ የተሰማሩ የሰራዊት አባላት ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤቶችን ገንብተው አስረከቡ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) በሰሜን ወሎ የግዳጅ ቀጠና የተሰማራው የሰራዊት አባላት በአካባቢያቸው ለሚኖሩ አራት አቅመ ደካማ እማወራዎች የመኖሪያ ቤት ገንብተው አስረክበዋል።

በርክክብ ስነስርአቱ ላይ የዕዙ አዛዥ እንዲሁም የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደሪ ዲያቆን ተስፋዬ ባታብል ተገኝተዋል።

የዕዙ ዋና አዛዥ እንደተናገሩት ሰራዊቱ ሀገርንና ህዝብን ከጥፋት ለመታደግ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ ከመሆኑም በላይ በልማት ስራዎች ላይ ተሳታፊ ነው ብለዋል። ለአቅመ ደካማዎች የሚያደረገውን ድጋፍም አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

የዞኑ አስተዳዳሪ በበኩላቸው ሰራዊቱ በአካባቢው ሰላምን ከማረጋገጥ ባሻገር ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በልማቱም እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ለቤቶቹ ግንባታ ከ9 መቶ ሺሕ ብር በላይ ወጪ የተደረገ መሆኑን የገለፁት የክፍለ ጦር አዛዥ እንዳሉት የሰራዊት አባላቱ በራሳቸው ተነሳሽነት ቤቶችን ገንብተው ማስረከባቸውን እና በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው 13 አባወራዎችን ቤቶች ለማደስ የጉልበት ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

ሠራዊቱ የተቸገሩ ወገኖችን የመርዳት ባህል አለው ያሉት የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ የአልባሳት፣ የመመገቢያ እና የምግብ ቁሳቁሶችንም ድጋፍ አድርጓል ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ አመላክቷል፡፡

ድጋፋ ከተደረገላቸው መካከልም ወይዘሮ አስረሴ ካሳው በሰጡት አስተያት የሰራዊት አባላቱ ባደረገላቸው ድጋፍ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውንና ችግራቸውንም የቀረፈላቸው መሆኑን ተናግረዋል።