ነሐሴ 15/2014 (ዋልታ) በሃገር መከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ እዝ የሰራዊት አባላት ድጋፍ በሰቆጣ ከተማ የዲጅታል ቤተ መጻሕፍት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።
የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የዳሎል ማዕከላዊ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ እንዳሉት የሰራዊት አባላቱ በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ለሕዝብ የቆሙ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረ ነው።
በዚህም የዳሎል ማእከላዊ እዝ የሰራዊት አባላት ከወር ደመወዛቸው በማዋጣት በሰቆጣ ከተማ የሕዝብ ዲጅታል ቤተ መጻሕፍት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል ብለዋል።
የቤተ መጻሕፍቱ መገንባትም በአካባቢው ያሉ ተማሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ተወዳዳሪነታቸውንና ውጤታማነታቸውን ለማሳደግ ያግዛል ተብሏል።
ሰራዊቱ የሃገርን ሉዓላዊነት ከማስከበር ባሻገር የሕዝብን ችግር ለይቶ በማውጣት ድጋፍ እያደረገ ይገኛልም ሲሉ ገልፀዋል።
ሰራዊቱ ከሕዝብ አብራክ የወጣ እንደመሆኑ መጠን የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል አሁንም በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ስቡህ ገበያው በበኩላቸው ሰራዊቱ ሕዝባዊነቱን የሚያረጋግጡ ተግባራትን እየሰራ ነው ብለዋል።
በዛሬው እለትም በሰቆጣ ከተማ የሕዝብ ዲጅታል ቤተ መጻሕፍት ለመገንባት መሰረት ድንጋይ በመጣሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የሰራዊት አባላቱ ሕዝባዊነቱን በማጠናከር የአቅመ ደካማ ቤቶችን መገንባትና መደገፍ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የዋግ ሕዝብም ለሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመሰረት ድንጋዩ በማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት ላይም ከሃገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች ባሻገር የክልሉና የብሄረሰብ አስተዳደሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!