በሰባት ወራት ወደ ውጪ ከተላኩ የጨርቃጨርቅ ውጤቶች ከ87 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኘ

 

የካቲት 30 /2013 (ዋልታ) – ባለፉት ሰባት ወራት ወደተለያዩ አገሮች ከተላኩ የጨርቃጨርቅ ስፌት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ምርቶች ከ87 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሪ መገኘቱን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ይህን ያስታወቀው የሰባት ወር ዕቅድ አፈጻጸሙን በቢሾፍቱ ከተማ በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኮቪድ-19 በጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳርፎ ቆይቷል፡፡

በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የኮቪድ-19 ተጽእኖን ተቋቁመው ምርታቸውን እንዲያሳድጉ በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት በአገሪቱ የሚገኙ የጨርቃጨርቅ ስፌት ኢንዱስትሪዎች ወደ ውጪ ከላኩት የጨርቃጨርቅ ስፌት ዘርፍ ምርት ከ87 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሪ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የግል ባለሃብቶችን በመደገፍ ሰራተኞቻቸው በክህሎትና በእውቀት እንዲበቁ ከማድረግ አንጻርም የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ሰባት ወራትም ከስምንት ሺህ በላይ ለሆኑ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትም የጥናትና ምርምር ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በስራ ዕድል ፈጠራ በሰባት ወራቱ ለ5 ሺህ 647 ዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጠር ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡