በሰብኣዊ መብት ጥሰት ምርመራ የተመላከቱ ምክረሐሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ሥራ ተጀመረ

ኅዳር 20/2014 (ዋልታ) በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ጦርነት አውድ የተፈጸሙ የሰብኣዊ መብት ጥሰት ምርመራ ላይ የተመላከቱ ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ ጸደቀ፡፡
መንግሥት አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማስቻል እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚኒሰቴሮች ግብረኃይልን ማቋቋሙ ይታወቃል።
ግብረኃይሉ በኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በጋራ በተደረገው ምርመራ ላይ የተመላከቱ ምክረሐሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የተጠቃለለ ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሃግብር በማጽደቅ ሥራውን ዛሬ ጀምሯል።
በዚህም የወንጀል ምርመራ እና ክስን፣ የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ጉዳዮችን፣ የጾታዊ ጥቃቶችን እና የሃብት ማሰባሰብን አስመልክቶ ሥራዎችን የሚያስተባበሩ አራት ኮሚቴዎችን ማዋቀሩን በወጣው መግለጫ አመላክቷል።
ኮሚቴዎቹ በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በሰላም ሚኒስቴር፣ በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እና በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመሩ ይሆናል፡፡
ግብረኃይሉ ትኩረታቸው ተጎጂዎች እውነትን የማወቅ እና ፍትሕ የማግኘት መብቶቻቸው አንዲከበሩ እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እና ካሳ የሚያገኙበትን ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንዲያተኩሩ ኮሚሽኑ አቅጣጫ አስቀምጧል።