ነሐሴ 10/2013 (ዋልታ) – በሱማሌ ክልል ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ትስስር በመፍጠር ሁከትና ግጭት ለማስነሳት የተደረገው ሙከራ በህብረተሰቡና በጸጥታ አካላት የጋራ ጥምረት መክሸፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ሁከትና ግጭቱን ለማስነሳት ሙከራ ያደረጉት ሃይሎች በኢትዮጵያ ብሎም በሱማሌ ክልል የመጣው ለውጥ ጥቅማቸውን ያስቀረባቸው ሃይሎች ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ትስስር ፈጥረው እንደሆነ የፖሊስ ኮሚሽኑ ገልጿል።
አሸባሪው ህውሓት ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የሱማሌ ክልል ሕዝብን አብረውት ሲዘርፉና ሲያዘርፉ የነበሩና ለውጥ ከመጣ በኋላ ከስልጣን የተወገዱ የቀድሞ አስተዳደር ርዝራዦች ከህውሓት ተልእኮ በመቀበል በክልሉ የሀይማኖት እና የጎሳ ግጭት በመፍጠር የከተማ ውስጥ አመፅ ለማቀጣጠል ሲሞክሩ እንደተደረሰባቸው ፖሊስ ጠቁሟል።
እንዲሁም በሶማሌና በኦሮሞ መካከል ግጭት እንዲነሳ ለማድረግ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበርም ማስታወቁን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።