በሳምንት 5.2 ሚሊየን ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል – የዓለም ጤና ድርጅት

ሚያዚያ 13/ 2013 (ዋልታ) – የዓለም ጤና ድርጅት ባለፉት ስምንት ተከታታይ ሳምንታት በዓለም ዙሪያ የኮቪድ-19 ስርጭት በሚያስደነግጥ ፍጥነት እጨመረ መምጣቱን ገልጿል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በጄኔቫ በሰጡት መግለጫ ባሳለፍነው ሳምንት 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች በአለም ላይ በኮቪድ-19 መያዛቸው የገለጹ ሲሆን ቁጥሩ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የተመዘገበ ትልቅ ቁጥር ነው ብለዋል፡፡
የሟቾች ቁጥር 3 ሚሊየን ማለፉን ዋና ዳይሬክተሩ አንስተው ለአምስት ተከታታይ ሳምንታት በከፍተኛ ቁጥር ጨምሯል ብለዋል፡፡
ዶክተር ቴድሮስ አገራት ለዜጎቻቸው የኮቪድ-19 ክትባትን ቢሰጡም የቫይረሱ የስርጭት መጠን እየተፋጠነ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄውን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንዲያጠናክር አስጠንቅቀዋል፡፡
ለአደጋ ተጋጭ የሆኑ ሰዎች ክትባቱን እየወሰዱ እንደመሆናቸው የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ መጠን ወደ ወጣትና ጎልማሶች ሊሸጋገር ይችላል ማለታቸውን ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 59 ዓመት መካከል በሚገኙ ሰዎች ስርጭቱ አስጊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡