በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከረመዳን ጾም በፊት ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ ተገለጸ

መጋቢት 12/2014 (ዋልታ) በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የእስልምና እምነት ተከታዮች ረመዳን ጾም ከመግባቱ በፊት ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደሚጀምሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ የሚያመቻችና የሚከታተል የመንግሥት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ሳዑዲ አረቢያ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ለመመለስ ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛልም ብለዋል።

አምባሳደር ዲና ባለፈው ሳምንት በነበራቸው ሳምንታዊ መግለጫ በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ እስካሁን 35 ሺሕ ዜጎች መመዝገባቸውንና ተገቢው ማጣራት እየተካሄደ መሆኑን መግለጻቸው ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል፡፡