በሴካፋ የሴቶች ሻምፒየንስ ሊግ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ 2ኛውን የምድብ ጨዋታ ያደርጋል

ነሐሴ 12/2014 (ዋልታ) በሴካፋ የሴቶች ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ሁለተኛውን የምድብ ጨዋታ ከቡሩንዲው ፎፊላ ክለብ ጋር ያደርጋል፡፡

በታንዛኒያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የሴካፋ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ላይ ኢትዮጵያን የወከለው ንግድ ባንክ በመጀመሪያ ዙር ጨዋታ የዛንዚባሩን ዋሪየር ኪዊንን ገጥሞ 9 ለባዶ ማሸነፉ የሚታወስ ነው፡፡

ጨዋታው ዛሬ 10 ሰዓት በታንዛኒያ አዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም የሚካሄድ ሲሆን ንግድ ባንክ ቡድን ማሸነፍ የሚችል ከሆነ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፉን ያረጋግጣል፡፡

በዚህ ውድድር ሎዛ አበራ እና መዲና አወል ከወዲሁ የውድድሩን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡

በውድድሩ አሸናፊ የሚሆን ቡድን በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ሴቶች ሻምፒየንስ ሊግ ላይ ምስራቅ አፍሪካን የሚወክል ይሆናል፡፡

በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው የሚመራው ቡድኑ ባሳለፍነው ውድድር ዓመት ለዋንጫ ጨዋታ ደርሶ በኬንያው ቪጋ ኪዊንስ መሸነፉ የሚታወስ ነው፡፡

በሀብታሙ ገደቤ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW