በኢትዮጵያ የስራ ሁኔታ ተቆጣጣሪ ዘርፍ ላይ የቴክኖሎጂ እና የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት እንዳለበት ተገለጸ፡፡
ከሰባት ክልሎች እና ከአንድ ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ለስራ ሁኔታ ተቆጣጣሪዎች በአሰሪና ሰራተኛ ህግ፣ በስራ ሁኔታ ቁጥጥር አገልግሎት፣ በስራ ቦታ አደጋና የአደጋ ስጋት ምርመራ፣ በህፃናት ጉልበት ብዝበዛ እና በግል ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ሽፋን ዙሪያ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
በሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሰሪና ሰራተና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ዘርፉ የቴክኖሎጂ እና የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት እንዳለበት ገልጸው፣ መንግስት ቴክኖሎጂን በማዘመን እና ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የስልጠናው ድጋፍ ሰጭ የሆነው የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ሱጋሞ በበኩላቸው፣ ወርልድ ቪዥን ባለፉት ስምንት አመታት ዘርፉን ለማጠናከር ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው፣ በተለይ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለማስቀረት እና የስራ ሁኔታ ተቆጣጣሪዎችን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
በስልጠናው ላይ የተሳተፉና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ዘርፉ በአዋጅ የተደነገጉ ህጎችን ለማስፈጸም እና የሰራተኞችን የስራ ላይ ደህንነት ለማረጋገጥ መንግስት የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
(በአካሉ ጴጥሮስ)