በስድስት ወራት ከ996 ሚሊየን ብር በላይ ለመንግስት መመለሱ ተገለፀ

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – የፌደራል እና የክልል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች በ2013 የመጀመሪያ ግማሽ በጀት ዓመት ባደረጉት የሙስና መከላከል ሥራ ከ996 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብና ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለመንግስት ተመላሽ እንዲሆን አድርገዋል፡፡

የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖቹ በ2013 የመጀመሪያ ግመሽ በጀት ዓመት ባደረጉት የሙስና መከላከል ሥራ በመደበኛ የአሰራር ሥርዓት ጥናትና በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራዎች በርካታ ገንዘብና ንብረት ከብክነት ለማዳን መቻላቸውን የተቋማቱ የ6 ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አመላክቷል፡፡

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ከክልል ኮሚሽኖች ጋር በተሰራው ሥራ ከ462 ሚሊዮን 157 ሺህ 600 ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ በምርመራና ክስ እንዲሁም ከ522 ሚሊዮን 631 ሺህ 100 ብር በላይ ደግሞ በተደረገ አስቸኳይ ጥናትና በአስተዳደራዊ መንገድ ከዝርፊያ ማዳን እና ማስመለስ ተችሏል ተብሏል፡፡

ከ9 ሚሊዮን 844 ሺህ 400 ብር በላይ ከቅጣት የተገኘ ሲሆን በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎች በሕገ ወጥ መንገድ የተወረረ ከ24 ሺህ 570 ሄክታር በላይ መሬት፣ 18 የቀበሌ ቤቶች እንዲሁም ለእርዳታ የመጣ 274 ኩንታል እህል ከሙሰኞች የማስመለስ ስራ መሰራቱን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡