ኅዳር 1/2015 (ዋልታ) በሶማሊያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ማሀድ ሞሐመድ የተመራ ልዑክ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርን (ኢመደአ) ጎበኘ፡፡
ልዑኩ በኢመደአ በነበረው ጉብኝት የኢንፎርሜሽን እና ኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማት ደኅንነት በማረጋገጥ በኩል በአስተዳደሩ እየተሰሩ ያሉ የቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ሥራዎችን እንዲሁም የኢትዮ ሳይበር ታለንት ልማት ማዕከልን ተመልክቷል፡፡
ልዑካን ቡድኑ ኢመደአ ከውጭ የቴክኖሎጂ ጥገኝነት በመላቀቅ ሀገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን በማረጋገጥ በኩል ሰፋፊ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ ገልጸው በቀጣይም ቀጣናዊ የሳይበር ደኅንነት ለማረጋገጥ በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታው ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚደረጉ የመረጃ ልውውጦች፣ በአቅም ግንባታ መስኮች እንዲሁም ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በሚደረጉ የጋራ ስምሪቶች ዙሪያ የተለያዩ ምክክሮችን እንደሚያደርግ ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
የሶማሊያ የመረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ከፍተኛ የልዑክ ቡድን ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት በትላንትናው እለት አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW