በሶማሌ ክልል የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የድጋፍ ጥሪ ቀረበ

የሶማሌ ክልል ሰላምና አንድነት ምክር ቤት

ኅዳር 30/2014 (ዋልታ) የሶማሌ ክልል ሰላምና አንድነት ምክር ቤት በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱ በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የክልሉ ኅዝብ በተፈጥሮ ድርቅ አደጋ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወንድሞቻቸውን ባላቸው ነገር እንዲያግዙና በድርቅ የተጎዱ አቅመ ደካማ የሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲረዱ ነው ጥሪ ያቀረበው።

በተጨማሪም ዳያስፖራው ማኅበረሰብ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው የተፈጥሮ  ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በሚደረገው ድጋፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ነው መልዕክት የተላለፈው፡፡

በተመሳሳይ ግብረሰናይ ድርጅቶች በድርቅ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚደረገው ድጋፍ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረቡን ከሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡