ሚያዚያ 1/2014 (ዋልታ) በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን ሁለት ወረዳዎች 260 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችሉ አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።
በዞኑ ዶሎ አዶና ቆልማዩ ወረዳዎች የተገነቡት የመሰኖ አውታር ፕሮጀክቶቹ 51 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አብዲቃድር ኢማን (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ኃላፊው እንዳሉት ፕሮጀክቶቹ ከፊል አርብቶ አደር የሆኑ ከ1 ሺሕ በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የማድረግ አቅም ያላቸው ናቸው።
ከገናሌ ወንዝ በመጥለፍ የተገነቡት የመስኖ ፕሮጀክቶች ዋናው ካናል እና ንዑስ ማካፋፈያ ካናል ጨምሮ አራት የውሃ ሞተሮችና የጎርፍ መከላከያ ባካተተ መልኩ መሰራታቸውን አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቶቹ ግንባታቸው ባለፈው ዓመት ተጀምረው ዘንድሮ የተጠናቀቁ ሲሆን በዞኑ የሚገኙ ከፊል አርብቶ አደር ነዋሪዎችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ በማድረግ የነበረባቸውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዙ ናቸው ተብሏል።
በአሁኑ ወቅትም ከፊል አርብቶ አደሮቹ የመስኖ አውታሮቹን ተጠቅመው የበቆሎ ሰብልና የተለያዩ አትክልቶችን ማልማት መጀመራቸውን ኃላፊው አብራርተዋል።
የሊበን ዞን ዋና አስተዳዳሪ መሐመድ መሁመድ በበኩላቸው በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የተገነቡ ፕሮጀክቶች በቆልማዩ ወረዳ መልካ ዲዳና ሰብላዩ ቀበሌዎች እንዲሁም በዶሎ አዶ ወረዳ ኮሌና ኩሊ ክሊምሳንጎ ቀበሌዎች ከፊል አርብቶ አደር ነዋሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚረዱ ናቸው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ 9 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ በተዘረጋው “ካናል” አማካኝነት 260 ሄክታር መሬት ማልማት እንደሚያስችሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።