በሶስት ወራት ከ3 ሺሕ 8 መቶ ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል ማመንጨት መቻሉ ተገለጸ

ኅዳር 15/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት 3 ሺሕ 898 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማመንጨቱን አስታወቀ፡፡

በተቋሙ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈፃሚ እያየሁ ሁንዴሳ እንደገለጹት በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 4 ሺሕ 783 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ 3 ሺሕ 898 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማመንጨት ተችሏል፡፡

በዚህም 3 ሺሕ 778 ነጥብ 5 ጌጋ ዋት ሰዓት ከውሃ፣ 108 ነጥብ 4 ጌጋ ዋት ሰዓት ከንፋስ እንዲሁም 10 ነጥብ 7 ጊጋ ዋት ዋት ሰዓቱ ከደረቅ ቆሻሻ የመነጨ ነው ተብሏል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በስራ ላይ ከሚገኙት 21 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ውስጥ ጢስ አባይ 2ኛ፣ ቆቃ፣ ጊቤ 3፣ አዋሽ 2ኛ እና 3ኛ እንዲሁም አዳማ 2 የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎች ከታቀደላቸው በላይ ኃይል እንዳመነጩ ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል፡፡

የተሻለ ኃይል ማመንጨት በቻሉት ጣቢያዎች ይስተዋል የነበረው የመለዋወጫ ዕቃ አቅርቦት መፍትሄ በማግኘቱና በዩኒቶቻቸው ላይ የጥገና ስራ በመከናወኑ ጣቢያዎቹ በሙሉ አቅማቸው ኃይል በማመንጨት አፈጻፀማቸው ከዕቅድ በላይ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

በአንፃሩ አመርቲ ነሼ፣ መልከ ዋከና፣ ጊቤ 1 እና 2፣ ፊንጫ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና አዳማ 1 የንፋስ ማመንጫ ጣቢያ እንዲሁም ረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ያመነጫሉ ተብሎ ከታቀደላቸው በታች ካመነጩ ጣቢያዎች መካከል ተጠቃሾች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት 19 ሺሕ 875 ነጥብ 9 ጌጋ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ዕቅድ መያዙንም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡