በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 110 ወጣቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩ ነው

መጋቢት 20/2014 (ዋልታ) በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከተመዘገቡ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ውስጥ 110 ወጣቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሰማርተው እንዲሰሩ መደረጋቸው ተገለጸ፡፡

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲና ለቴክኒክ እና ሙያ ተመራቂ ተማሪዎች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት እያካሄደ ይገኛል።

ስልጠናውን የወሰዱት ወጣቶች ተደራጅተው በ22 ኢንተርፕራይዞች ውስጥ ገብተው እንደሚሰሩ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ገልፀዋል።

ስልጠናውን የወሰዱት ወጣቶች ውጤታማ እንዲሆኑ መንግሥት እና የጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) በጋራ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል፡፡

ወጣቶቹ በተሰማሩበት ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሻማ፣ ሳሙና፣ ዘይት፣ ካልሲ እና ሌሎችም  ምርቶችን የሚያመርቱ ሲሆን የመጀመሪያ ምርታቸውም በተለያየ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡

በሜሮን መስፍን