በበዓል ወቅት የኃይል መቆራረጥን ለመፍታት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንተከናወኑ ነው

ሚያዝያ 12/2014 (ዋልታ) የትንሳኤና የኢድ-አልፈጥር በዓላት መቃረባቸውን ተከትሎ ሊኖር የሚችለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር ለመፍታት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ተቋሙ በበዓላቱ ዋዜማና ዕለት የኤሌክትሪክ ኃይል ሳይቆራረጥና ሳይዋዥቅ ለማቅረብ አስቀድሞ የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጾ ችግሩ ከተከሰተ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የአስቸኳይ ጥገና ግብርኃይል አዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱን አስተውቋል፡፡

መሰል ዝግጅቶች ቢደረጉም በተለይ በመጪው የትንሳኤ በዓል አሁንም መቆራረጥ ሊከሰት ስለሚችል ከሲሚንቶ ፋብሪካዎችና ወደ ውጭ ከሚልኩ ኢንዱስትሪዎች በስተቀር ሁሉም ኢንዱስትሪዎች በበዓሉ ዋዜማ ከምሽቱ 12 ሰዓት  ጀምሮ እስከ በዓሉ ዕለት ቀን 6 ሰዓት  ድረስ ከዋናው የኃይል ቋት (ግሪድ) የሚያገኙትን የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ ለሙሉ ባለመጠቀም የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ተቋሙ ጠይቋል።

ደንበኞችም በቤት ውስጥ የሚገለገሉባቸውን የኤሌክትሪክ ቁሶች ኃይል ቆጣቢ እንዲሆኑ፤ ሲጠቀሙም ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ እንዲሆን ያስፈልጋል ነው ያለው፡፡

እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት በተለይም ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት ባለው ጊዜ ቢጠቀሙ የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማግኘት ባለፈ የኤሌክትሪክ መቆራረጥን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል በሚቋረጥበት ጊዜ የጥገና ሥራ ለማከናወን የተቋሙን መታወቂያ የያዙ የቴክኒክ ባለሙያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ለሥራ ጉዳይ እንደሚንቀሳቀሱ ኅብረተሰቡ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግና የተቋሙ የጥገና ሰራተኞች በመምሰል መሠረተ ልማቱ ላይ ስርቆትና ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም ደንበኞች ማንኛውንም መረጃዎች ለመጠየቅ፣ ጥቆማዎችና አስተያየቶች ለማቅረብ ወደ አቅራቢያቸው የሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ ወይም በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል ማሳወቅ ይችላሉ ብሏል።

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!