በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሮል

                           የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር -ንጉሱ ጥላሁን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2013 (ዋልታ)- በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ የ2013 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ ፈጠራ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እየተካሄደ ባለው የውይይት መድረክ እያቀረበ ነው።

በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን የግማሽ ዓመቱን የስራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ አፈጻጸም አቅርበዋል።

በበጀት ዓመቱ ለ3 ሚሊዮን ዜጎች፤ በግማሽ ዓመቱ ደግሞ ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልፀዋል።

ዕቅዱ በዘርፎች ሲከፋፈል በግብርና 44 በመቶ፣ በኢንዱስትሪ 32 በመቶ፣ በአገልግሎት 24 በመቶ እንደሆነ ዘርዝረዋል።

ከዚህም ውስጥ 80 በመቶው ቋሚ፣ 20 በመቶ ጊዜያዊ የስራ ዕድል መሆኑንም አስረድተዋል።

የስራ ዕድል ፈጠራው የጾታ ስብጥር ለወንዶችና ለሴቶች እኩል 50 በመቶ መሆኑንም አክለዋል።

ከዚህ አንጻር በአገራዊ የስራ ዕድል ፈጠራ የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ከ1 ነጥን 6 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር የዓመቱን ዕቅድ 56 በመቶ መፈፀም ተችሏል ብለዋል።

አፈጻጸሙ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 49 በመቶ ጭማሪ አለው ተብሏል።

አፈጻጸሙ በዘርፍ ሲታይም በግብርና 30 በመቶ፣ በኢንዱስትሪ 26 በመቶ፣ በአገልግሎት ደግሞ 44 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ተብራርቷል።

ከዚህ ውስጥ ቋሚ የስራ ዕድል 62 በመቶ ሲሆን ጊዜያዊ 38 በመቶ እንደሆነም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በጾታ ስብጥር በወንዶች የዕቅዱ 65 በመቶ ሲሳካ በሴቶች 35 በመቶ ማሳካት ተችሏል።

የዕቅዱ አፈጻጸም በአጠቃላይ ሲታይ የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ከዕቅድ በላይ ማሳካታቸው ተገልጿል።

የደቡብ፣ የሲዳማና የሀረሪ ክልሎች ከፍተኛ አፈጻጸም ሲያስመዘግቡ የድሬዳዋ አስተዳደርና የሱማሌ ክልል መካከለኛ አፈጻጸም ያሳዩ ናቸው።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የጋምቤላና የአፋር ከልሎች ደግሞ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳዩ መሆናቸውን ኢዜአ በዘገባው አስታውቋል።