በቡራዩ ከተማ ለአርሶ አደሮችና ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት እውቅና ተሰጠ

ግንቦት 13/2014 (ዋልታ) በቡራዩ ከተማ ለአርሶ አደሮች እና ወደ ባለሃብትነት ለተለወጡ የጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት እውቅና ተሰጠ።

የቡራዩ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አለምነሽ ገደፋ በዛሬው እለት ለ91 አርሶ አደሮችና ለ45 ወደ ባለሃብትነት የተሻገሩ የአነስተኛን ጥቃቅና ማኅበራት እውቅና መስጠቱን ገልፀዋል።

ወደ እንቨስትመንት የተሻገሩት አካላት በ264 ነጥብ 35 ሚሊየን ካፒታል 43 ነጥብ 35 ሄክታር መሬት ያለማሉም ተብሏል።

በዛሬው እለት እውቅና የተሰጣቸው አካላትም በሥራቸው ለ5 ሺሕ 126 ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

አርሶ አደር ጥለን የሚገኝ አንዳችም ጥቅም የለም ያሉት የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዲሱ ከበደ አርሶ አደሮቻችን መሬታቸውን እንዲያለሙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለብን ብለዋል።

በዛሬው እለት እውቅና የተሰጣቸው አርሶ አደሮችም በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር እየሰራን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው አርሶ አደሮችም የተሰጣቸውን አደራ ለሌላ ሦስተኛ ወገን ማሳለፍ እንደሌለባቸውና በራሳቸው ጥረት መሬታቸው ላይ መስራት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

በታምራት ደለሊ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW