በባሌ ዞን ሐረና ቡሉቅ ወረዳ የአሸባሪው ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

ነሀሴ 21/2013 (ዋልታ) – በባሌ ዞን ሐረና ቡሉቅ ወረዳ የአሸባሪው ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ።
በባሌ ዞን ሐረና ቡሉቅ ወረዳ ሦስት የአሸባሪው ሸኔ አባላት በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እና በፀጥታ አካላት የተቀናጀ ሥራ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና በሕዝቡ ላይ በመተኮስ ጉዳት ለማድረስ በሞከሩ ሁለቱ ላይ ደግሞ እርምጃ መወሰዱን የባሌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የሸኔ የሽብር ቡድን አባላት በተደጋጋሚ ወደ ዞኑ ለመግባት ሙከራ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የባሌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ጄይላን አሚን ተናግረዋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት የሽብር ቡድኑ አባላት፣ “የኦሮሞን ሕዝብ ትክክለኛ ፍላጎት እንዳልተረዳን ያወቅነው ሕዝቡ በአንድነት ወጥቶ ቁጥጥር ስር ሲያውለን ነው” ብለዋል።
“ሌሎች የተቀሩት ወጣቶችም ይህንኑ ሐቅ ሊረዱ ይገባል” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
የወረዳው ነዋሪዎች በበኩላቸው የኦሮሞን ሕዝብ ለ27 ዓመታት ሲገድል፣ ሲያኮላሽ እና ከሀገሩ እንዲሰደድ ሲያደርግ የቆየውን ወያኔን መቼም የማንቀበለው በመሆኑ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የአሸባሪዎቹን ሴራ የማክሸፍ ሥራ ሠርተናል ብለዋል።
የሐረና ቡሉቅ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ሙሐመድ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማድነቅ መሰል እርምጃዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ጠይቀዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።