በባሕር ዳር 18 ሺሕ 772 ህገ ወጥ ጥይት ከነተጠርጣሪዎች መያዙን ፖሊስ አሰታወቀ

በባሕር ዳር 18 ሺሕ 772 ህገ ወጥ ጥይት ከነተጠርጣሪዎች መያዙ
በባሕር ዳር 18 ሺሕ 772 ህገ ወጥ ጥይት ከነተጠርጣሪዎች መያዙ

የካቲት 22/2014 (ዋልታ) በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ዳግማዊ ምኒሊክ ክፍለ ከተማ 18 ሺሕ 772 ህገ ወጥ ጥይት ከሦስት ተጠርጣሪ ግለሰቦች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማዋ አስተዳደር ፖለስ መምሪያ የማኅበረሰብ ዐቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ዋጋው ታረቀኝ እንደገለጹት ህገ ወጥ ጥይቱ በቁጥጥር ስር የዋለው ትናንት ረፋድ ላይ ነው።
በክፍለ ከተማው ማር ዘነብ ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ ቤት ተከራይቶ የሚኖር አንድ ግለሰብ ቆሻሻ ካርቶን ሲያቃጥል ሾልኮ የቀረ ጥይት በመፈንዳቱ ለህገ ወጥ ጥይቶቹ መያዝ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
ፍንዳታውን ተከትሎ ግለሰቡ ሁለት ባጃጆችን ጠርቶ ግማሹን ተተኳሽ ጥይት ጭኖ ለመንቀሳቀስ ሲሞክር በአካባቢው በሥራ ላይ የነበሩና ፍንዳታውን የሰሙ የፀጥታ ኃይሎች ከነጥይቱ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተናግረዋል።
በባጃጆቹ ውስጥ ያለው ጥይት ከተያዘ በኋላ ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት ውስጥ በተካሄደ ፍተሻ ተጨማሪ ተተኳሽ ጥይት መገኘቱን ኮማንደር ዋጋው አመልክተዋል።
በባጃጆችና በቤት ውስጥ በተደረገ ፍተሻም 5 ሺሕ 150 የብሬን እና 13 ሺሕ 622 የክላሺንኮቭ ተተኳሽ ጥይት ሊያዝ መቻሉን አስረድተዋል።
በወንጀል ድርጊቱ ተጠርጣሪ ግለሰቡና ሁለት የባጃጅ አሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄድ መሆኑንም የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል፡፡