መጋቢት 6/2014 (ዋልታ) በባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መሆናቸው ተገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ቢልቱማ ቂጣታ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል የአገርን ኢኮኖሚ ወደ ኋላ ከማስቀረቱም በተጨማሪ በከተማዋ ያለውን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲስተጓጎል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በ2013 እና 2014 በጀት ዓመት በድምሩ 12 ሺሕ 708 ሜትር የሚረዝም የኬብል ስርቆት ተፈፅሞ በተቋሙ ላይ ከ20 ሚሊዮን 733 ሺሕ ብር በላይ የሚገመት ኪሳራ መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ይጠቁማል፡፡
በዚህም የማጣራት ሥራ በመስራት ተጠርጣሪዎችን በፖሊስ ቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡