በቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት

መጋቢት 14/2014 (ዋልታ) በቤልግሬድ 18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት።

የልዑካን ቡድኑ ዛሬ ጠዋት ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የስፖርት ፌዴሬሽኖች ፕሬዝዳንቶች አቀባበል አድርገውለታል።

ለልዑካን ቡድኑ አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ የአበባ ጉንጉን የተበረከተ ሲሆን የመከላከያ ማርሽ ባንድ እና የአገር ፍቅር ቴአትር ቡድን የተለያዩ ጥዑመ ዜማዎች በማቅረብ አቀባበሉን አድምቀውታል።

ቡድኑ በተመረጡ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በቱሪስት አውቶቡስ እንደሚዘዋወርና በሸራተን አዲስ ወደተዘጋጀው የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት የማበርከት ሥነ ሥርዓት እንደሚኖር ተገልጿል።

የቤልግሬድ 2022 የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናን ኢትዮጵያ በ9 ሜዳሊያ ከዓለም አንደኛ በመሆን ውድድሩን ማጠናቀቋ ይታወቃል።

በሀብታሙ ገደቤ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW