በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና ጋር በአቻ ተለያየ

መጋቢት 29/2015 (ዋልታ) የ18ኛ ሳምንት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ መርኃ ግብር ዛሬ ሲጀምር ሻፒዮኑን ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሲዳማ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ በተከናወነው በዚህ ጨዋታ ሲዳማ ቡና 3ኛ ደቂቃ ላይ ፊሊፕ አድጃህ ባስቆጠራት ግብ መምራት ቢችልም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ቅዱስ ጊዮርጊስን ዳግማዊ አርአያ አቻ የሚያደርገውን ግብ አስቆጥሮ ነጥብ ተጋርቶ ወትቷል፡፡

በአብዛኛው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሲዳማ ቡናዎች ጥንቃቄ በተሞላበት መልሶ ማጥቃት ጨዋታ ግቦችን ለመፍጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንጻራዊነት ካለፉት ጨዋታዎች ከባድ የሚባል ፈተና የገጠመው ሲሆን የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲቸገርም ተስተውሏል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ18 ጨዋታ 39 ነጥብ በመያዝ የአንደኝነት ደረጃውን ሲያስጠብቅ ሲዳማ ቡና በበኩሉ በ20 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ በሊጉ ነገ ባህርዳር ከተማ ከፋሲል ከነማ የሚያከናውኑት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

 

በሀብታሙ ገደቤ