በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የኩርሙክ ወርቅ ፕሮጀክት ልማት ግንባታ ተጀመረ

ሚያዚያ 08/2013 (ዋልታ) – በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በ355 ሚሊዮን ዶላር የኩርሙክ የወርቅ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ተጀምሯል፡፡

የፕሮጀክቱን ግንባታ የማአድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ርእሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በጋራ አስጀምረውታል።

የወርቅ ማምረቻው ስራ ሲጀምር በአመት 7500 ኪሎግራም ወርቅ እንደሚያመርት የተገለጸ ሲሆን፤ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ማምረቻው ወደ ስራ እንደሚገባ ከማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በ355 ሚሊየን ዶላር ወጪ የሚደረግበት ፕሮጀክቱ ከ750 በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድልን የሚፈጥር ይሆናል በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በሚከናወንበት አካባቢ ከፍተኛ የወርቅ ምርት እንዳለ በጥናትና በናሙና በመረጋገጡ ሌሎች ቀጣይ ክፍሎች የሚኖሩት ይሆናል ተብሏል።

በአጠቃላይ ማምረቻው ወደ ስራ ሲገባ በአመት የሚያመርተው 7 ቶን የወርቅ ምርት የሀገሪቱን የወርቅ ማምረት አቅምና የውጪ ምንዛሪ ገቢውን በከፍተኛ መጠን እንደሚያሳድግ ተገልጿል፡፡