“በብሔር ስም እየነገዱ ኢትዮጵያን ማሸበር ፈጽሞ አይቻልም” ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ኅዳር 17/2014 (ዋልታ) “ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመንዛትና በብሔር ስም በመነገድ ኢትዮጵያን ማሸበር ፈጽሞ አይቻልም” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአሸባሪ ቡድኖችን የሽብር ተልዕኮ ማክሸፍ የኢትዮጵያዊያን የኅልውና ጉዳይ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

ከንቲባዋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከኢትዮጵያ ባለፈ የአፍሪካ ርዕሰ መዲናና የዓለም ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባ በፕሮፓጋንዳ ለማሸበር የሚደረጉ ጥረቶች የኅልውና ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት የነበሩ ናቸው ብለዋል።

ከሳምንታት በፊት የውስጥና የውጭ ኃይሎች አዲስ አበባ ስለመከበቧ ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ ቢቆዩም፣ አዲስ አበባ ዛሬም ያለምንም ኮሽታ ዕለታዊ ክዋኔዋን መቀጠሏን ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስተዳደሩ ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የከተማዋን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡

ሕብረተሰቡ በሚያደርገረው ከፍተኛ እገዛና ትብብር ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ ከባድ የጦር ሜዳ መሳሪያዎች፣ ተቀጣጣይና ፈንጂ ቁሳቁሶች እነዲሁም የሽብር ተግባር ለመፈጸም በህቡ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በከተማዋ ጊዜያዊም ሆነ መደበኛ መታወቂያ መስጠት የተከለከለ መሆኑን አሳስቧል፡፡

የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ከተከራየበት ቤት ማስለቀቅ እንደማይቻል ከዚህ ቀደም የተላለፈው ውሳኔ ለቀጣይ 3 ወራት እንዲፀናም ተወስኗል ብሏል፡፡