በቦሌ ክፍለ ከተማ በተደረገ ብርበራ የጦር መሳሪያዎች እና የመገናኛ ሬደዮኖች ተያዙ

ኅዳር 12/2014 (ዋልታ) በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ቤቶች ላይ በተደረገ ብርበራ 5 ክላሽን- ኮቭ ጠብመንጃ እና 6 ሽጉጦች ከነተተኳሾቻቸው እንዲሁም 2 የእጅ መገናኛ ሬዲዮ እና ሌሎች ንብረቶችን መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች መካከል አንደኛው ክላሽን- ኮቭ ጠብመንጃ በዕድሳት ምክንያት ተዘግቷል በተባለ ፔንሲዮን ግቢ ውስጥ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ የተቀመጠ ሲሆን መገናኛ ሬዲዮዎቹ ደግሞ በፔንሲዮኑ ኮርኒስ ውስጥ ተደብቀው የተያዙ ናቸው፡፡
ፖሊስም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሰረት በማድረግ ኅዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው ብርበራ 2 የእጅ መገናኛ ሬዲዮ በፔንሲዮኑ ኮርኒስ ውስጥ በፌስታል ተጠቅልለው ተደብቀው ተገኝተዋል።
አንድ ክላሽን- ኮቭ ጠብመንጃ ከ19 ጥይት ጋር በሸራ ተጠቅልሎ ግቢው ውስጥ በሚገኝ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ መያዙንም ፖሊስ አስታውቋል። በፔኔሲዮኑ ውስጥ ምንም አይነት ዕድሳት እየተደረገ አለመሆኑንም ፖሊስ አረጋግጧል፡፡
በተመሳሳይ በክፍለ ከተማው ወረዳ 3 የሕወሓት እና ሸኔ የሽብር ቡድኖችን በተለያየ መንገድ ይደግፋሉ ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ላይ በተደረገ ብርበራ 4 ክላሽን- ኮቭ ጠብመንጃ ከ140 ጥይት ጋር፣ 6 ሽጉጥ ከ65 ጥይት ጋር እንዲሁም አንድ የእጅ ቦንብ በቁጥጥር ስር ውሎ በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ ፖሊስ አስታውቋል።
አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ ለሚገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች የአዲስ አበባ ፖሊስ ምስጋናውን እያቀረበ ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት እያስገኘ ያለው ውጤት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቁን ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።