በቦረና ዞን ለተቸገሩ ዜጎች ከ36 ሺሕ ኩንታል በላይ እህል ተከፋፈለ

ኅዳር 4/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች ከ36 ሺሕ ኩንታል በላይ እህል መከፋፈሉን የኦሮሚያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራርና የልማት ተነሺ ኮሚሽን ገለፀ።
መንግሥት በድርቁ ምክንያት በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ 100 ሚሊዮን ብር መድቦ እየሰራ ነው።
ከተመደበው ገንዘብ እስከ አሁን 10 ሚሊዮን ብር ለከብቶች መኖ፣ 20 ሚሊዮን ብር ለውሃ አቅርቦት መዋሉን ምክትል ኮሚሽነር ገረመው ኦሊቃ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ከተመደበው ገንዘብ በተጨማሪ 30 ሚሊዮን ብር ለውሃ አቅርቦት እና 20 ሚሊዮን ብር ለሳር ግዥ እንዲውልም ወስኗል።
በዝናብ እጥረቱ ምክንያት የተጎዱ ከ166 ሺሕ በላይ ወገኖች በተለየ ሁኔታ ተጨማሪ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ገልጸው ከ8 ሺሕ በላይ እንስሳት ጉዳት እንደደረሰባቸውም ለኢዜአ ተናግረዋል።
በክልሉ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ተጨማሪ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ከ300 ሺሕ በላይ ዜጎች መኖራቸው ተገልጿል።