በተለያዩ አካባቢዎች ለሰራዊቱ የሚደረገው ድጋፍ እንደቀጠለ ነው

ሐምሌ 26/2013 (ዋልታ) – በተለያ አካባቢዎች ለመከላከያ ሰራዊቱ የገንዘብና ዓይነት ድጋፎች እንዲሁም የድጋፍ ሰልፎች እንደቀጠሉ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማይፀብሪ ግንባር ለሚገኙት ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ 34 የእርድ ሰንጋ እና 446 በጎችና ፍየሎችን አስረክቧል፡፡

ድጋፉን የተረከበት የምዕራብ ዕዝ ስንቅ ዕደላ ሃላፊ ሌ/ኮሎኔል አሸብር ሽፈራው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከሠራዊቱ ጋር መሆኑን ተናግረው ከተማ አስተዳደሩ ላደረገው ድጋፍ በሠራዊቱ ስም አመስግነዋል፡፡

በተመሳሳይ የወልድያ ከተማ ወጣቶች ከ150 ሺህ ብር በላይ በማውጣት በራያ ግንባር ለተሰለፈው መከላከያ ሰራዊት የለስላሳ መጠጦችን አቅርበዋል።

ድጋፉን ከተቀበሉት የሰራዊቱ አመራሮች መካከል በ12ኛ ክፍለ ጦር የአንደኛ ብርጌድ 3ኛ ሻለቃ ዋና አዛዥ ሻለቃ ኤፍሬም የትሻወርቅ ከተዋጊው ሃይል ጋር ግንባር ድረስ አብሮ የሚዘምት ወጣት ከጎናችን ይዘን አሸባሪው የህውሃት ቡድንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ድል እናደርገዋለን ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልግል በለስና የፓዌ ከተማ ነዋሪዎች የአሸባሪውን የህውሀት ሀገር የማፍረስ ሴራ የሚያወግዝና ለኢፌዴሪ መከላከያ  ሠራዊት የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል።

በሰልፉ ላይ ሰራዊቱ እያካሄደ ያለውን የህልውና ዘመቻ የሚደግፉና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ልዩ ልዩ  መፈክሮች መስተጋባታቸውን ከመከላከያ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡