በተለያዩ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ለተመደቡ ዲፕሎማቶች የስራ መመሪያ ተሰጠ

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በተለያዩ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሚሲዮኖች ለተመደቡ የዳያስፖራ ክላስተር አስተባባሪዎችና ዲፕሎማቶች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ስምሪቱን ለልዩ ተልዕኮ ዲፕሎማቶችን መመደብ በማስፈለጉ የተካሄደና ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚኒሲቴር መ/ቤቱን የሰው ኃይል አቅምን ከግንዛቤ ወስጥ በማስገባት ለዳያስፖራ ስራዎች ዲፕሎማቶቹ መመደባቸውን አብራርተዋል።

በተያያዘም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያጎድፉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ አካላት እንዳሉ አንስተው፤ ተመዳቢ ዲፕሎማቶቹም ሆነ ሌሎች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ዲፕሎማቶች በየአገራቱ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በመተባበር የሀገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታን ለማስገንዘብ እንዲቻል ለዲጅታል ዲፕሎማሲ ስራዎች ትኩረት በመስጠት ስራቸውን ማከናውን አንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው ዲፕሎማቶቹ የዳያስፖራውን የሀዝን እና ደስታ ጊዚያት በቅርበት እንዲካፈሉ ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።