በተመድ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ውጤታማ ነበር- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

መስከረም 20/2014 (ዋልታ) – በ76ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተሳተፈው ልዑክ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማስረዳት ረገድ ውጤታማ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ያለፉትን ሁለት ሣምንታት የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብትና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ተግባራትን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በጉባዔው ስለነበረው ተሳትፎ አስረድተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር መወያየታቸውንም ገልጸዋል።

በሕዳሴ ግድብ፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሁኔታና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተም ማስረዳታቸውንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

“የሠብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የሚያስፈልገው በትግራይ ብቻ ሳይሆን በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ አማካኝነት በአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ በርካታ ዜጎች እንደሆነም አስረድተዋል” ብለዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፍ የሠብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች ይህንኑ ተረድተው ድጋፍ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውንና ድርጅቶቹም አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በውይይቶቹ ላይ የተሳተፉ መሪዎች ‘የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት የማይነካ’ ስለመሆኑ ማንሳታቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።