በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ መሰጠቱ እንደቀጠለ ተገለጸ

ነሐሴ 6/2014 (ዋልታ) በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እና ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ድጋፍ መሰጠቱ እንደቀጠለ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል በቦረና፣ ምስራቅ ባሌ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ምስራቅ ጉጂ እና ምዕራብ ሃረርጌ ዞን ለሚገኙ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በድርቅ የተጎዱ ወገኖች ከ1 ሚሊዮን 5 መቶ ሺሕ  በላይ ኩንታል የምግብ ድጋፍ መደረጉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ድጋፎቹ ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ ከአለም ባንክ፣ ከአጋር አካላት፣ ከክልሉ እና ከኅብረተሰቡ የተገኘ መሆኑ ኃላፊው ገልጸዋል።

በተጨማሪም፤ ለ1 ሚሊዮን 33 ሺሕ ዜጎች በጥሬ ገንዘብ ከ973 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

በሶማሌ ክልል ለ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የምግብ ድጋፍ መደረጉን እና ከ819 ሚሊዮን በላይ የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከ1 ቢሊዮን 284 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዝብ ድጋፍ ለክልሉ መደረጉን አቶ ደበበ ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢብኮ ነው።

ለደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልም 314 ሺሕ ኩንታል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች መከፋፈሉንም ተናግረዋል።