በቱኒዚያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከስልጣናቸው ተነሱ

በቱኒዚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ

ሐምሌ 19/2013 (ዋልታ) – በመላው ቱኒዚያ የተቀሰቀሰውን ከፍተኛ አመጽ ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣና አንስተው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ደግሞ ማገዳቸው ተገለጸ።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች መንግሥት ወረርሽኙን ለመግታት የወሰደውን እርምጃ በመቃወም አደባባይ ወጥተው ቁጣቸውን የገለጹ ሲሆን፣ እሁድ ዕለት ደግሞ ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸው ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ካኢስ ሳኤድ በሀገሪቱ መረጋጋትን ለመፍጠር እሰራለሁ ካሉ በኋላ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሾሙ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማሰናበታቸው እና ምክር ቤቱን ማገዳቸው ከመፈንቅለ መንግሥት ተይቶ አይታይም እያሉ ነው።

ፕሬዝዳንቱ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት “እነዚህን እርምጃዎች የወሰድነው በአገሪቱ ሰላም እስከሚመለስና አገሪቱን ማዳን እንድንችል በማሰብ ነው” ብለዋል።

ትናንት ዕሁድ ምሽት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ሂኬም ሚቺቺ ከኃላፊነታቸው የመነሳት ዜና ከተሰማ በኋላ ዜጎች አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በዋና ከተማዋ ቱኒዝ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚዎችን ተቀላቅለው መታየታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።

ፕሬዝዳንቱ ምንም እንኳን በዋና ከተማዋ ወጥተው ከተቃዋሚ ሰልፈኞች ጋር አብረው ቢታዩም፤ ከዚህ በኋላ አላስፈላጊ አመጽ የሚቀጥል ከሆነ መከላከያ ኃይል ጣልቃ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል።

“ማንኛውም ዜጋ የጦር መሳሪያ የሚጠቀም ከሆነ፣ ጥይት የሚተኩስ ከሆነ የመከላከያ አባላት በጥይት ምላሽ ይሰጣሉ” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች በተለያዩ ከተሞች ዋና ዋና ጎዳናዎች በመሰባሰብ የገዢው ፓርቲ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ሲገልጹ ተስተውለዋል። በርካቶችም የፓርቲው አመራሮች ይውጡልን በማለት ፓርላማውም እንዲፈርስ ጠይቀዋል።

የጸጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎች ወደ ፓርላማው ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ ሲከለክሉና ወደ ‘ቦርጊባ’ አደባባይ እንዳይሄዱ መንገድ ሲዘጉ ተስተውለዋል። ይህ ጎዳና በአውሮፓውያኑ 2011 ለተቀጣጠለው ጸረ መንግሥት ተቃውሞ ዋነኛ ማዕከል ሆኖ አገልግሎ ነበር።

ፖሊስ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ጭምር የተጠቀመ ሲሆን፣ አንዳንድ ሰዎችን ደግሞ በቁጥጥር ስር አውሏል። ይህን ተከትሎም ተቃውሞውም ወደ አብዛኛው የአገሪቱ ከተሞች ተስፋፍቷል።

ቱኒዚያ አሁንም ድረስ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ በአፍሪካም በኮሮናቫይረስ በእጅጉ ከተጠቁት አገራት መካከል ትገኝበታለች።