በታንዛኒያ እስር ቤት የነበሩ 126 ኢትዮጵያዊያን ተመለሱ

ሐምሌ 11/2014 (ዋልታ) በታንዛኒያ እስር ላይ የነበሩ 126 ኢትዮጵያዊያን ከእስር ተፈተው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተገለጸ፡፡

ታንዛኒያን አቋርጦ ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚደረግ ህገ-ወጥ ጉዞ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በታንዛኒያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እየዋሉ ለእስር እንደሚዳረጉ ይታወቃል።

ከነዚህም መካከል በሁለተኛው ዙር 126 ኢትዮጵያዊያን በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአገሪቱ ከሚገኘው የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመቀናጀት ወደ ኢትዮጵያ መሸኘታቸው ተጠቁሟል።

የተቀሩትም በቀጣይ በተቀመጠላቸው የጉዞ ፕሮግራም መሠረት ወደ አገር ቤት መመለስ እንዲችሉ እየተሰራ ይገኛል::

በርካታ ኢትዮጵያዊያን በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በመታለል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከፍለው እጅግ አደገኛ የሆነ ህገ ወጥ ጉዞ የሚያደርጉ ሲሆን በመንገዳቸው ላይ ለርሃብ፣ እስር፣ ስቃይ ብሎም ለሞት እንደሚዳረጉ በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ከዚህ ቀደም በመጀመሪያ ዙር ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም 20 ዕድሜያቸው ከ11 እስከ 17 የሚሆኑ በታንዛኒያ በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር የቆዩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW