በትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ

ግንቦት 19/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ ትናንት ከሌሊቱ 10:00 ሰዓት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ገለጸ።

በአደጋው በሁለት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱንና የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን የኤጀንሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የእናትና ልጅ ህይወት ማለፉን የጣርማ በር ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

አደጋው አስፍቸው ቀበሌ ልዩ ቦታው ጭራሜዳ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የደረሰ መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ሸዋታጠቅ ኃይለስላሴ ተናግረዋል።

ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ባቲ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበረ አምቡላንስ ተሽከርካሪ መንገድ ዳር መኪና በመጠበቅ ላይ የነበሩ እናትና ልጅ ገጭቶ ህይወታቸው ማለፉንም ነው የተናገሩት። ዋና ኢንስፔክተሩ አያይዘውም በአደጋው ሁለት ሰዎች ላይ ቀላል አደጋ ደርሷል ብለዋል፡፡

አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሎ በህግ ከለላ ውስጥ እንደሚገኝና የአደጋው መንስዔ እየተጣራ መሆኑን የጣርማ በር ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW