በኢትዮጵያ ለሚገኙ የልማት አጋሮች ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በትግራይ ክልል ህግ ለማስከበር ከተወሰደው እርምጃ በኋላ የክልሉን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ስለተደረገው እርምጃ በገንዘብ ሚኒስትሩ በአቶ አህመድ ሺዴ እና በሰላም ሚኒስትሯ በወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ዛሬ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
አቶ አህመድ ህግ የማስከበር እርምጃው የሰላማዊ ሰዎችን ህይወት ለአደጋ በማያጋልጥ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ እርዳታ ጥረቱን በመደገፍ ረገድ የልማት አጋሮች ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አድንቀዋል፡፡ ሁሉም የልማት አጋሮች ኢትዮጵያ የቀጠናው የሰላም ማእከል እንድትሆን ከጎኗ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አያይዘውም በትግራይ ክልል ሓላፊነት በማይሰማው ወንጀለኛው ቡድን የወደሙትን የትራንስፖርት፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮሙዩኒኬሽን መሠረተ-ልማቶችን በመጠገን ክልሉን መልሶ በማቋቋም ወደ ነበረበት የመመለስ ጉዞ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
የመሠረተ ልማቶቹ መውደም ምግብ እና መድኃኒት የመሳሰሉትን የሰብአዊ ድጋፎችን ለማድረስ ጊዜያዊ ድልድዮችን በአስቸኳይ መገንባት የጠየቀ በመሆኑ በሰብአዊ ድጋፉ ምላሽ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩንም አመልክተዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም የከተማ አስተዳደሮችን በማዋቀር ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይ መዋቅር በመዘርጋት የተሻለ የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነትና አፈጻጸም እንዲኖር ቁልፍ ሚና መጫወቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በቅንጅት የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ለትግራይ ክልል እና ጉዳት በደረሰባቸው አጎራባች የአማራና የዐፋር ክልሎች ሲያከናውን መቆየቱን አስረድተዋል፡፡
በአንዳንድ ወረዳዎች የባንክ አገልግሎት በመጀመሩ፣ በአካባቢ ላሉ ገበያዎች አስፈላጊ ሸቀጦች ተደራሽ እንዲሆኑ ጥረት በመደረጉ እና የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለ1.8 ሚሊዮን የክልሉ ህብረተሰብ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ማድረግ በመቻሉ በክልሉ ሕይወት ወደ ቀድሞው ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
የልማት አጋሮች ድጋፍ ቡድን 30 ዓለም አቀፍ በይነ መንግስታት እና የመንግስታት ትብብር የልማት አጋሮችን ያቀፈ ቡድን ሲሆን፣ ዓላማውም በኢትዮጵያ የፖሊሲ ውይይት እንዲጎለብት እና የልማት አጋሮች ድጋፍ ውጤታማ እንዲሆን ማስተባበር እንዲሁም በብሔራዊ ፕላን እና ዘላቂ ልማት ግቦች ላይ የክትትል እና ግምምገማ ተግባሮችን ማከናወን መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡