በትግራይ ክልል ከ700 ሺህ በላይ ህዝብ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት በዘመቻ ተሰጠ

ሰኔ 12/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል 13 ወረዳዎች እና የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ከ700 ሺህ ለሚበልጥ ህዝብ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መሰጠቱ ተገለጸ።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ቃል አቀባይ ዶክተር አደዳ ሃይለስላሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ ከትባቱ ለህዝቡ የተሰጠው ከሰኔ 05/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አምስት ቀናት ነው።

ክትባቱን ያገኙት በክልሉ ሁለት ሚሊየን ያህል ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከተያዘው እቅድ ውስጥ መሆኑን ገልጸው፣ ቀሪዎቹን ለማዳረስም በሚቀጥሉት ቀናት እንዲከተቡ ዘመቻው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻን ለማሳካት የጤና ሚኒስቴር ለክልሉ ጤና ቢሮ የጤና ባለሙያዎችና የተለያዩ የመድሃኒቶችን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

በክረምቱ ወራት ለማካሄድ በተያዘው ሁለተኛው ዙር ክትባትም ለተጨማሪ ሁለት ሚሊየን ዜጎች ለመስጠት መታቀዱን ዶክተር አደዳ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ከሽሬ እንደስላሴ እስከ ማይጨው ድረስ ባሉ መስመሮች ለ91 ሺህ ያህል ዜጎች ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት መሰጠቱንም አመልክተዋል።

ክትባቱን ላልወሰዱ ዜጎችም በቀጣይ ሁለት  ወራት ውስጥ የሚሰጥ መሆኑን ዶክተር አደዳ አስታውቀዋል።